የሚጥል በሽታ (Epilepsy; ኤፕለፕሲ)

 የሚጥል በሽታ (Epilepsy; ኤፕለፕሲ)

አጠቃላይ እይታ

✍️የሚጥል በሽታ (ኤፕለፕሲ) የረዥም ጊዜ (ሥር የሰደደ) ተላላፊ ያልሆነ የነርቭ (የአንጎል) በሽታ ሲሆን፣ በተጎዱ የአንጎል ሴሎች በሚፈጠር ያልተለመደ የአንጎል የኤሌክትሪክ ንዝረት ጊዜያዊ የነርቭ ሥርዓት መታወክ  ምክንያት ተደጋጋሚ የአንጎል መናድ (epileptic seizures) ያስከትላል

ክስተቱም ከጥቂት ሴኮንዶች እስከ 3 ደቂቃዎች የሚቆይ መፍዘዝ፣ ራስን መሳት፣ ከቁጥጥር ውጪ የሆነ ማንቀጥቀጥ ፣ የጡንቻ መገታተር ብሎም ታማሚው እንዲወድቅ ያደረጋል። አንድ ሰዉ የሚጥል በሽታ አለዉ ተብሎ የሚወሰነዉ በ 24 ሰዓታት ልዩነት ቢያንስ ሁለት ወይም ከዚያ በላይ ያልተቀሰቀሱ የሚጥል መናድ  (unprovoked seizures) ተደጋግሞ ሲከሰት ነዉ።

የሚጥል በሽታ በሁሉም የዕድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ሰዎችን የሚያጠቃ ሲሆን በዓለም ዙሪያ ወደ 50 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች የሚጥል በሽታ አለባቸው፡፡ የሚጥል በሽታ ያለባቸው ሰዎች ወደ 80% የሚጠጉት ዝቅተኛ እና መካከለኛ ገቢ ባላቸው አገሮች ውስጥ ይኖራሉ። በኢትዮጵያ ውስጥ ከ1000 ሰዎች መካከል 5 ሰዎች ወይም ከሩብ ሚሊዮን በላይ ሰዎች የሚጥል በሽታ እንዳለባቸው ይገመታል።

የሚጥል በሽታ በንክኪ፣ በምራቅ፣ ህመምተኛውን በመርዳት አይተላለፍም፡፡

የሚጥል በሽታ በፈጣሪ ቁጣ፣ እርግማን ወይም እርኩስ መንፈስ የሚመጣ አይደለም፡፡ ስለዚህ የሚጥል በሽታ ያለባቸው ሰዎችን እና ቤተሰቦቻቸውን ማግለልና አድልኦ ማድረግ ተገቢ አይደለም።

 ✋የሚጥል በሽታ መንስዔዎች

የሚጥል በሽታ ካለባቸው ግማሽ ያህሉ ውስጥ መንስዔው  እስካሁን አይታወቅም ፡፡ ለሚጥል በሽታ ከሚያጋልጡ መንስዔዎች  መካከል ጥቂቶቹ  የሚከተሉትን ያካትታሉ፡፡

🎯በቅድመ ወሊድ እንዲሁም በወሊድ ጊዜ በተራዘመና አስቸጋሪ ምጥ ወቅት በህፃኑ ላይ በሚደርስ የአንጎል ጉዳት   

🎯ተፈጥሮአዊ በሆነ የአንጎል  እክል 

🎯ከባድ የጭንቅላት ጉዳት

🎯የአንጎል ኢንፌክሽን ለምሳሌ ማጅራት ገትር 

🎯 የአንጎል ዕጢ 

🎯 ስትሮክ

🎯በዘር የሚመጣ 

የሚጥል በሽታ ምልክቶች

የሚጥል በሽታ ምልክቶች የሚከተሉትን ሊያካትቱ ይችላሉ።

👉 እስከ 3 ደቂቃዎች የሚቆይ ጠቅላላ የሰዉነት ማንቀጥቀጥ እና ከዚህ ጋር ተያይዞ ራስን መሳትና መውደቅ፣ ዓይን ወደላይ መስቀል፣ አረፋ መድፈቅ ፣ ላይ ላዩን መተንፈስ እና ሽንት ማምለጥ፡፡ ታማሚው ከነቃ በኋላ የሆነውን ነገር ለማወቅ እና ለማስታወስ ይሳነዋል፣ ራስ ምታትም ሊኖርው ይችላል። 

👉ኢፕለፕሲ በብዛት የሚጥል በሽታ በመባል የሚታወቅ ቢሆንም ሳይጥል የሚከተሉትን ምልክቶች ሊያሳይ ይችላል፡፡ 

·   በድንገት መደነጋገር፣ መፍዘዝ ፣ ግንዛቤ ማጣት፣ያለማስተዋል ማፍጠጥ

·   ሳያስቡ መራመድ፣የት እንዳሉ መርሳት   

·   ደጋግሞ አላማ የሌለው የእጅና የሰውነት እንቅስቃሴዎች ማሳየት ፡፡ ለምሳሌ ከንፈር መምጠጥ፣ ዕቃዎችን በተደጋጋሚ ማንሳት ወይም ልብሶችን መሳብ

🤚ለሚጥል በሽታ የሚደረጉ ምርመራዎች

የታማሚው የሕክምና ታሪክ ለሚጥል በሽታ ምርመራ መሠረት ነው። ሐኪሙ ስለህመሙ ክስተት ሙሉ መረጃ ይፈልጋል። የሚጥል በሽታ ያጋጠማቸው ሰዎች ብዙውን ጊዜ የሆነውን ስለማያስታውሱ፣ ክስተቱን ያዩ የቤተሰብ አባላት ወይም ሌሎች ሰዎች ለሐኪሙ ማስረዳት አለባቸው። 

በታማሚው የሕክምና ታሪክ ላይ በመመሥረት የሚከተሉት የምርመራ አይነቶች ሊታዘዙ ይችላሉ።

👉የደም ናሙና ምርመራዎች 

👉 ኤሌክትሮኢንሴፋሎግራፊ (ኢኢጂ፤ EEG) መደበኛ ወይም ያልተለመደ የአንጎል የኤሌክትሪክ እንቅስቃሴ ያሳያል።

👉ኤምአርአይ (MRI) ወይም ሲቲ ስካን (CT scan) የአንጎል መዋቅራዊ እክሎችን፤  የአንጎል ዕጢ እና የአንጎል ጠባሳችን ሊያሳዩ ይችላሉ።

 የሚጥል በሽታ ሕክምና

የሚጥል በሽታ በሕክምና መቆጣጠር ይቻላል። አንዳንድ የሚጥል በሽታ ሙሉበሙሉ ባይድንም ከመቶ 70 እጅ በሐኪም የሚታዘዙ መድኃኒቶችን በተገቢው መንገድ በመጠቀም በቁጥጥር ስር ሊውል ይቻላል።

ከበሽታው በህክምና ጥሩ ለውጥ ለማግኘት በሐኪሙ ምክር መሰረት ክትትል ማድረግ ያስፈልጋል።

 👍 ለሚጥል በሽታ ተጠቂ ግለሰቦች ጠቃሚ ምክሮች

👉በቂ እንቅልፍ ማግኘት፤አለመጨነቅ፡፡

👉ከአልኮል መጠጦችና እና ሌሎች አደንዛዥ እጾችን መጠቀመም መቆጠብ ህመሙ እነዳይቀሰቀስ ያደርጋል፡፡ 

👉 ለአደጋ ከሚያጋልጡ ቦታዎች ለምሳሌ ከእሳት እና ገደል አጠገብ፤ ከከባድ ማሽኖች መራቅ አለባቸው፡፡

👉በዋና ከመዝናናትና መኪና ከማሽከርከር መቆጠብ አለባቸው፡፡

👉  በሐኪም የታዘዙ መድሀኒቶችን ያለ ሐኪም እውቅና ማቋረጥ ለህመሙ ማገርሸትን ስለሚያስከትል መድሀኒቶችን ላለማቋረጥ ጥንቃቄ ማድረግ፡፡ 

🤚ለሚጥል በሽታ የመጀመሪያ ዕርዳታ አሰጣጥ

በሚጥል በሽታ ሳቢያ የማንቀጥቀጥና ሕሊናን የመሳት ሁኔታ ያጋጠመውን ሰው ለመርዳት የሚከተሉትን መንገዶች መጠቀም ያስፈልጋል፡፡ 

👉በጎን በኩል እንዲተኙ መርዳት 

👉 በጭንቅላት ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ትራስ ማንተራስ 

👉 አንገት አካባቢ የታሰረ ማንኛውም ዓይነት ልብስ ወይም ጌጥ ማላላት 

👉በአካባቢ ጉዳት ሊያደርሱ የሚችሉ ቁሳቁሶችን ማስገድ 

👉ሰውዬው አደጋ ላይ ካልሆነ በቀር አስጨንቆ አለመያዝ

👉 አፉ ውስጥ ባዕድ ነገር አለማስገባት ወይም አፉን እንዲከፍት አለመታገል

👉መንፈራገጡ እስከሚያቆም ድረስ እና ሙሉ በሙሉ ንቁ እስኪሆን ድረስ ከሰውየው ጋር ይቆዩ

👉 ክብሪት ወይም ማንኛውንም አይነት ጭስ አለማሸተት

ውድ ቤተሰቦች ምልክቶችን ቀድሞ በመገንዘብ  በሽታው የመጣል ደረጃ ላይ ሳይደርስ ጥንቃቀቄ ማድረግ እና ሳይባባስ ህክምና ማድረግ አስፈላጊ ነው::

የሚጥል በሽታ (Epilepsy; ኤፕለፕሲ) የሚጥል በሽታ (Epilepsy; ኤፕለፕሲ) Reviewed by Ayduwan on March 02, 2023 Rating: 5

No comments:

Powered by Blogger.